ኢህአዴግ ሞተ! ኢህአዴግ ነገሰ! ለሞትነው እዘኑ! ለነገስነው ተደሰቱ! (ዘሞትነ ንህነ፣ ወዘነገስነ ንህነ፣ ሕዘኑ ወለዘሞትነ፣
ተፈስሁ ወለነገስነ) የሚል በረከተ - አዋጅ ከእንጦጦ ተሰማ። በአዋጁ መሰረት ሳይሆን፣
በባህላችን መሰረት ለቀድሞ አለቃዬ እስከ ሳልስት ሃዘን ተቀምጫለሁ። መለስ በስልጣን ዘመኑ ለሰራው ሃጢአት አምላክ ነፍሱን ይቅር
ይላት ዘንድም ተመኝቻለሁ። እንግዲህ ከሳልስት በሁዋላ ህይወት ትቀጥላለች.....
መቼም በመለስ ዜናዊ መሞት
“ህዝቡ ሁሉ” ማዘኑ እውነት ሆኖአል። መቶ ሰዎች ሆ! ብለው ሰልፍ ከወጡ፣ “ህዝቡ!” ናቸው። ቤታቸው ቁጭ ያሉት ሌሎች መቶ
ሰዎች ለጊዜው፣ “ህዝቡ” አይደሉም። ቢሆንም በመለስ ዜናዊ ሞት፣ “ህዝቡ” አዝኖአል። በግዴታ ጥቁር እንዲለብሱ የተገደዱ
ቢኖሩም፣ በፈቃዳቸው ደረት የሚደቁ፣ ሙሾ የሚያወርዱና ጥቁር የለበሱም አሉ። አማረ አረጋዊ በሪፖርተር ርእሰ አንቀፁ እንዳሰፈረው
ደግሞ፣ “የኢትዮጵያ ህዝብ ወርቅ ህዝብ መሆኑን አስመስክሮአል”። በአማረ ቀመር በመለስ ሞት ያላዘኑ ጨርቅ ሆነው ቀርተዋል።
“ለሟች ማዘን ባህላችን
ነው” የሚሉ አሉ። “...ኢህአዴግ የህዝቡን ይህን ባህል ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ አዋለው” ሲሉም አጥብቀው ይተቻሉ። ይህ በትእዛዝ
የማስለቀስ ነገር፣ “ከሰሜን ኮርያ የተኮረጀ ነው” የሚሉ አሉ። ምን ሩቅ አስኬደን? ጃንሆይ ለልጃቸውና ለባለቤታቸው ሞት
ተመሳሳይ ነገር ፈፅመዋል። በዚህም ተባለ በዚያ፣ “ህዝቡ” አዘነም አላዘነም፣ መለስ ዜናዊ አርፎአል። ላይመለስ ሄዶአል። “ቀጥሎ
ምን ይሆናል?” ሚለውን ጥያቄ መመለስ አንገብጋቢው ጉዳይ ነው።
መለስ ግማሹን የኢህአዴግ
አካል ይዞ መሞቱ ያፈጠጠ እውነት ለመሆን በቅቶአል። የህወሃት አመራር አባላት ለሁለት የመከፈላቸው ሹክሹክታ ያልተጣራ ቢሆንም፣
እውነት የመሆን እድሉን የሚጨምሩ መረጃዎች ብቅ እያሉ ነው። በኦሮሚያ - ኦህዴድ የሚታየው የስልጣን ክፍተት ከተደቀኑት አደጋዎች
አንዱ ነው። አዲሱ ለገሰ ወደ ብአዴን በሙሉ ሃይሉ እየተመለሰ መሆኑ ይሰማል። የመለስን ወንበር ለመተካት 23 አመታት በትእግስት
የጠበቀው ብአዴን አስጨናቂ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱን ማመን ይቻላል። ለብአዴን ሰዎች ከትችት ለመዳን ብቸኛው ማምለጫ ቀዳዳ
ሃይለማርያምን መሾም ቢሆንም፣ የሃይለማርያም ሹመት በራሱ መፍትሄ አያመጣም። ማንም በሩቅ ሊገምተው እንደሚችለው ሃይለማርያም
ስራውን ሊሰራው አይችልም። ስዩም መስፍን ወይም አባይ ፀሃዬ ከጀርባ ሆነው ስራውን ሊሰሩለትም ያስቸግራቸዋል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ
በአስቸኳይና በድንገት ውሳኔ የሚሹ ጉዳዮችን ሃይለማርያም ምን ያደርጋቸዋል? እንደ አስተርጓሚ ሆኖ ኢትዮጵያን የመሰለ ብዙ
ውስብስብ ችግር ያለበትን አገር በውክልና መምራት ይችላል? ከጀርባ የሚያዙትን በርካታ ዝሆኖች በምን አይነት ትእግስትና ማቻቻል
ያስተናግዳቸዋል?
በመሰረቱ መለስ የሌለበት
ኢህአዴግ ምን መልክ ይኖረዋል? በቀጣይ የአካባቢያችን የፖለቲካ የሃይል አሰላለፍ ምን ሊመስል ይችላል? የኢትዮጵያ ተቃዋሚ
ሃይላት ምን ማድረግ ይችላሉ? ምንስ ማድረግ አይችሉም? ይህን የመሰሉ የሚነሱ ውስብስብ ጥያቄዎች ማለቂያ የላቸውም። ከመለስ
ቀብር መልስ በአጭር ጊዜ ውስጥ መልስ የሚያገኙ ይመስለኛል።