Wednesday, August 29, 2012

መለስ ዜናዊ በማን ይተካል? (April 1 2012)

ወቅታዊውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ የሃይል አሰላለፍ በመገምገም፣ “መለስ ዜናዊ! – በማን ይተካል?” ለሚለው ጥያቄ ምላሽ መስጠት በርግጥ ቀላል አይደለም። በቅድሚያ ግን “በርግጥ መለስ ዜናዊ ስልጣኑን ይለቃል?” ብሎ መጠየቅ ይገባል። መለስ ዜናዊ፣ “ከሁዋላ ሆኜ ማገዜ ባይቀርም፣ እለቃለሁ” ብሎ ደጋግሞ ነግሮናል። ተቃዋሚዎች በበኩላቸው፣ “መለስ እለቃለሁ ቢልም ባይልም አፍንጫውን ተይዞ ይለቃል” ሲሉ ቁጣ ባዘለ ድምፅ እየገለፁ ነው። የሆነው ሆኖ በራሱ ፍላጎትም ሆነ ተገዶ መለስ ስልጣኑን መልቀቁ የማይቀር ከሆነ ቀጣዩ የኢትዮጵያ መሪ ማን ይሆናል? በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ ተንትኖ የፃፈ አላጋጠመኝም…

ስዬ እና ብርቱካን…?

ሁለቱ የፖለቲካ ሰዎች (አይን ካረፈባቸው) የቀጣዩ ዘመንየኢትዮጵያ መሪዎች መካከል መሆናቸው ይወሳል። መቼም አሜሪካኖች ለኛ ካላቸው የተቃጠለ ፍቅር የተነሳ፣ የአፍሪቃ ቀንድችግር ያሳስባቸዋል። በፖለቲካውም በረሃቡም መሃንዲስና በጎአድራጊናቸው። “የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ተጣምረው አንድ ሃይል መሆንአቃታቸው እንጂ ባገዝናቸው ነበር” ሲሉ ማማረራቸው ብዙ ጊዜ ይሰማል። ያሬድ ጥበቡ የበረከትን መፅሃፍ በተቸበት መጣጥፉ፣ “የስዬና የአሜሪካኖችን መቀራረብ” በጨረፍታ አጫውቶናል። በይስሃቅ ኤፍሬምና በብርቱካን ሚደቅሳ መካከል “የቀጠለው”ግንኙነትም እንዲሁ ርእሰወግ ሆኖ ሰነባብቶአል። የስዬ አብርሃ አስፈላጊነት በአሜሪካኖቹ ከታመነበት ቆየ። ስዬ በህወሃትና በተቃዋሚዎች መካከል ድልድይ እንዲሆንላቸው ይፈልጋሉ። ሰራዊቱንም እንደነበረ ያቆይላቸዋል። ጄኔራል ሳሞራን ከላይ ነጥሎ በማንሳትብቻ የሰራዊቱን መዋቅር እንደነበረ ለማስቀጠል፣ ስዬ ሁነኛ ምርጫቸው ነው። የከፋ ነገር ከመጣ መለስም ቢሆን በዚህ ይስማማል። ስዬን በቀጥታበመለስ ቦታ ማስቀመጡ ግን አስቸጋሪ ነው። ብርቱካን ከላይ ብትሆን ሚዛኑ ሊጠበቅ ይችላል። ሴት መሆኗ እና የገነባችው ስም፣ የወጣች በትማህበረሰብ ሁሉ ሚዛናዊ ያደርጋታል” ይላሉ። ማሰብ ችግር የለውም። ምን ችግር አለው?

ሃይሌና መሃመድ….?

ሃይሌ ገብረስላሴና መሃመድ አላሙዲ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን ያስቡይሆን? ሁለቱም ከጀርባ ግፊት አለባቸው። የኛ ሰው መቼም ክፉና ተንኮለኛ ነው። ከፈገግታ ጋር ወደ ጆሮ ጠጋ ብሎ ማሳሳት ይችልበታል። “ሼክ መሃመድ… ህዝቡ እኮ ‘እሳቸው ቢመሩን ይሻል ነበር’ እያለ ነው። ቢያስቡበት ጥሩ ነው…” “ሃይሊሻ! ለምን አትወዳደርም? የላይቤሪያው ጆርጅ ዊሃ እንኳ ተወዳድሮአል። ህዝቡ ግልብጥ ብሎ ነው የሚመርጥህ…” ታምራት ላይኔ ጠቅላይ ሚኒስትር በነበረ ጊዜ ይህንኑ የአላሙዲ ፍላጎት አጫውቶኝ ነበር። ቃለመጠይቅ አድርጌው ካበቃን በሁዋላ ስናወጋ፣ “የሼኩ የረጅም ጊዜ እቅዱ ወደ ፖለቲካው መግባት ነው። ከሆነለት አገሪቱን መምራት ይፈልጋል” ብሎ እንደነገረኝ አስታውሳለሁ። አሁን እንኳ አሳቡን ሳይለውጥ አልቀረም። በወርቅ ቁፋሮ ተጠምዶአል። ከእለታት አንድ ቀን የኢትዮጵያ ህዝብ ከእንቅልፉ ሲነቃ፣ ትልልቅ ባዶ ጉድጓዶችን ያገኛል። የሃይሌ ገብረስላሴን ጠቅላይ ሚኒስትር የመሆን ጉዳይ ለመለስ በጥያቄ መልክ አቅርበውለት ነበር። “…ይህን በተመለከተ ከሃይሌ ጋር አላወራንም” ሲል መልስ ሰጠ። አያያዘናም የማስጠንቀቂያ ወንድማዊ ቃል አከለበት፣ “….ሃይሌ ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ ውጤታማ ይሆናል ወይስ አይሆንም የሚለውን ለመፍረድአልችልም። ሆኖም ወደ ፖለቲካ የመግባት ሙሉ መብት አለው…” በውነቱ መለስ ሃይሌን ደግ መክሮታል። ሁለቱ ታዋቂ ሰዎች ከቀጣዩ ዘመን የጠቅላይ ሚኒስትርነት የስም ዝርዝር ላይ እጃቸውንም ሆነ ስማቸውን ባያስገቡ ይጠቅማቸዋል። ይልቁንመለስን በመምከርና ታሪካዊ ምርጫ አካሂዶ፣ ታሪክ እንዲሰራ ቢያግባቡት እነርሱንም ታሪክ ሲያስታውሳቸው ይኖራል።

እነ ተወልደ…?

“እነ ተወልደ” በሚል ተውላጠ ስም ከሚታወቁት መካከል እንደገና አንሰራርቶ ወደ ስልጣን የሚመለስ ሊኖር ይችላል? አይመስለኝም። እነ ተወልደ ከፖለቲካው ርቀዋል። ለነገሩ ባመለካከትም ተለያይተዋል። ልዩነታቸው በፈረደባት ኤርትራ ዙሪያ ነው። ተወልደ ከመለስ ጋር የከረረ እልህና ፀብ ቢኖረውም፣ በአሰብና በኤርትራ ሉአላዊነት አጀንዳ ላይ አሁንም በአቋሙ ላይ እንደፀና መሆኑ ይሰማል። የስዬ፣ የገብሩና የጆቤን ቅስቀሳ፣ እንደ ደጋፊ መፈለጊያ ብቻ የያዋል። አለምሰገድ ገብረአምላክና ሰለሞን ጢሞም በተመሳሳይ በተወልደ መንገድ በመጓዝ ላይ ናቸው። ቀሪዎቹ የህወሃት አንጋፋዎች ወደ ቢዝነሱ አለም ገብተዋል። ፃድቃንና ጃማይካ፣ “ራያ” የተባለውን ቢራ ለመገንባት እንቅልፍ አጥተዋል። ፃድቃን ከደቡብ ሱዳን ያገኘውን ገንዘብ ወደ ማሌዢያ ባለማሸሸቱ ሊመሰገን ይገባዋል። ሃይለኛ እና ተሳዳቢ የነበረው ቢተው በላይ እንኳ፣ እንዲህ ረግቦ በቢዝነሱ ላይ መወሰኑ ያስደንቃል። ታስሮ ከተፈታ ወዲህ ፀጥተኛ ሆኖአል። አሁን አሁን፣ እስርቤት ገብተው የሚወጡ ፖለቲከኞች ጠባያቸው ለምን እንደሚለወጥ ሊገባኝ አልቻለም። የሚወጓቸው መርፌ ይኖር ይሆን? በጥቅሉ እነ ተወልደ ከወደፊቷ ኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን ያነሱ ይመስላሉ። መልካም የጡረታ ዘመን እንመኝላቸዋለን።

ፍሰሃ እሸቱ….?

ፍሰሃ በግልፅ ቋንቋ፣ “ስልጣን አልፈልግም” ብሎ ተናግሮአል። አያይዞም፣ “እንደ ማርቲን ሉተር ኪንግ ነፃነት የሚገኝበትን አቋራጭ መንገድ ላሳያችሁ ነው የመጣሁት” ብሎናል። እንደ ፍሰሃ እቅድ በውጭ አገር የተበተኑትን እና በነገር ካራ ርስበርስ የሚወጋጉትን ተቃዋሚዎች በማስታረቅ በመጪው ሰኔ ወር ላይ አንድ ካውንስል ያቋቁማል። ከፖለቲካ ርቆ የተቀመጠውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ማንቀሳቀስ እንደሚችልም በርግጠኛነት አብራርቶአል። ያን ጊዜ፣ እንደ ፍስሃ ህልም 50 ሺህ ኢትዮጵያዊ ተቃዋሚ “እንደ ቆላ ወፍ – እንደ ግሪሳ” ዋሽንግተን ዲሲ ነጩ ቤተመንግስት ደጃፍ ላይ ይጥለቀለቃል። ይህ ሲፈፀም፣ አሜሪካና መላው አለም የኢትዮጵያን ህዝብ የነፃነትና የዴሞክራሲ ጥያቄ ማዳመጥ ይጀምራል። 50 ሺህ ተቃዋሚ እንደ ግሪሳ ዋሽንግተንን ሲያንቀጠቅጣት በኢትዮጵያም በተመሳሳይ አመፁ ይፈነዳል። እናም አፋኙ የመለስ ስርአት በመጪዎቹ ስድስት ወራት፣ (ከመስከረም 2012 ወዲህ) የስልጣን እድሜው ያበቃለታል። ካውንስሉም የሽግግር ሂደቱን ተረክቦ ቀጣዩን የምርጫ ስርአት ይዘረጋል።
መቸም ፍሰሃ እሸቱ በቃል እንዲህ ቀለል አድርጎ እንደተነተነው በተግባር መፈፀም ከቻለ፣ እሱ “ስልጣን አልፈልግም” ቢልም የኢትዮጵያ ህዝብ፣ አስገድዶ የጠቅላይ ሚኒስትርነቷን ወንበር ያስረክበዋል። እንግዲህ በቅርቡ ደግሞ “ከፍሰሃ ጀርባ እነ አጅሬዎቹ አሉ” የሚል ሹክሹክታ ያነበብኩ ይመስለኛል። ከሆነ በርግጥ ሊሳካለት ይችል ይሆናል። የሆነው ሆኖ ፍሰሃ ራሱን ከወደፊት እጩ መሪዎች አንዱ አድርጎ ፈጥሮአል…

ብርሃኑና አንዳርጋቸው…?

ብርሃኑ ነጋ እና ግንቦት 7 የስልጣን ፍላጎት እንደሌላቸው ገና ከመነሻው ግልፅ አድርገዋል። ይህን አባባል ግን ተቀብዬው አላውቅም። በፕሮግራማቸው መሰረት ትግሉን መርተው ድል ማድረጉ ከተሳካላቸው በወደፊቱ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሳይወዳደሩ ዳር ላይ ይቆማሉ ተብሎ አይታሰብም። እንደምናየው የተከተሉት የትግል አቅጣጫ ፈተና የበዛበት ሳይሆን አልቀረም። እንደ ድመት 9 ነፍስ ያላቸው ይመስል፣ የሞት ፍርድ ሜዳሊያ ተሸክመዋል። ከወያኔ እስርቤት የተከተቱ ብዙ አባላት አላቸው። በተግባርም ሆነ በፕሮፓጋንዳው ወያኔን በብርቱ እየተፈታተኑት ነው። የትጥቅ ትግል የሚከተሉ እንደመሆናቸው፣ ምን እየሰሩ እንዳሉ ማወቅ አይቻልም። ብዙውን ጊዜ ምን እየሰሩ እንዳሉ የሚነግረን ወያኔ ነው። “ሊገሉኝ ነበር – ያዝኳቸው! ሊያፈነዱ ነበር – አከሸፍኩት!” ይለናል። ከከማል – ኦነግ፣ ከአፋርና ከህብረብሄራዊ ድርጅቶች ጋር የጋራ ግብ ነድፈው በመጓዝ ላይ ናቸው። በመሆኑም ብርሃኑ እና አንዳርጋቸውም መጪዋን ኢትዮጵያ ለመረከብ አማራጭ ሆነው ይታያሉ…

አረጋዊና ግደይ…?

አረጋዊና ግደይ ህወሃትን መስርተው ሲያበቁ ከህወሃት ተባረሩ የፖለቲካ ሰዎች ናቸው። ስለሁለቱ ሰዎች ሳስብ በሚዲያ ብቻ ከሚያደርጉት አስተዋፅኦ ባሻገር፣ ለምን ወደ መሬት ወርደው እንደማይንቀሳቀሱ አላውቅም። “ደሚት” በሚል ስም የሚጠሩትን የትግራይ አማፅያን ለምን ማግኘት እንደማይፈልጉም አይገባኝም። በተጧጧፈው ትግል ውስጥ ሙሉ ተሳታፊ ሆነው አይሰሙኝም። ምርጫ ሲደርስ ብቅ ይላሉ። መልሰው ደግሞ እልም ይላሉ። አረጋዊ በርሄ መለስ እና ስብሃትን የሚተችበት እድል ካገኘ ብቅ ይላል። በተረፈ ብዙም የለም። ስርአቱን የሚያውቁት እንደመሆኑ ብዙ ማገዝ በቻሉ ነበር። ምናልባት አቻችለው መጓዝ ይፈልጉ ይሆናል። ግንባር መስመሩ ላይ አሉ ማለት ግን አይቻልም። ስለዚህ የትም የሉም…

ነጋሶ – በየነ- መረራ….?

በየነና መረራ ሸክማቸውን ስዬ አብርሃ ላይ ጭነው እረፍት የፈለጉ መስለው ታይተዋል። በየነ ጴጥሮስ ፕሬዚዳንት ግርማን ለመተካት ሞክሮ ከከሸፈበት ወዲህ ተስፋ ቆርጦአል። መረራ በንግግሩ ለወያኔ ጩቤ ቢሆንባቸውም፣ አሁን አሁን የአፍእላፊ ክሱን በመስጋት ቃላት በመምረጥ ሲጨናነቅ ይታያል። በፍርሃት ማሰሮ ውስጥ ተጨረማምቶ መቀመጥ ግዴታው የሆነ ፖለቲከኛ ምን አይነት ትግል ማድረግ ይቻለዋል? በርግጥ ጊዮርጊስ ከፈቀደ ሁለቱ አንጋፋዎች ወደፊት ሚኒስትር የመሆን እድል ይኖራቸው ይሆናል። መለስን ይተካሉ ብሎ የሚጠብቅ ግን ያለ አይመስልም።
ነጋሶ የዋህ ናቸው። የቅርብ የትግል ጓዳቸው አንዷለም አራጌ ታስሮ በጡጫና በእርግጫ ሲደበደብ እሳቸው፣ “በአንቀፅ 22 መሰረት..” የሚል አረፍተ ነገር ያለበት መግለጫ ሰጡ። ኢትዮጵያ ላይ ምን አንቀፅ አለ? ሌላው ቀርቶ አንቀፅ 39 እንኳ፣ ለህወሃት ስትራቴጂአዊ ፍላጎት ብቻ ተብሎ የገባ ነው። ዶክተር ነጋሶ አንቀፅ 22ን ከሚጠቅሱ፣ የብሉይ ኪዳን ህግን ቢጠቅሱ በተሻለ ነበር። ማለትም፣ “ለእርግጫ – እርግጫ! ለጡጫ – ጡጫ!” የሚለውን። ነጋሶ የወያኔን ህገመንግስት ያረቀቁት ከልባቸው ስለነበር፣ አሁንም ህጉ በስራ ላይ ያለ ይመስላቸዋል። ነጋሶ ይህን ያህል ዘመን ከህወሃት ጋር አብረው ሰርተው፣ የህወሃትን አንጎልና ልብ አለማወቃቸውን ሳስበው ግርም ይለኛል። የሆነው ሆኖ ነጋሶ ጊዳዳ ኢትዮጵያን ከመምራት አንፃር አማራጭ ናቸው ብዬ አላስብም። ታሪክ ግን፣ “ሰላምተኛ እና ጥሩ ሰው ነበሩ” በሚል ያስታውሳቸው ይሆናል።

ታማኝ በየነ…?

ታማኝ ኮሜዲያን በነበረበት ጊዜ በጣም ያስቀን ነበር። ከመነሻውም ግን ቀልዶቹ ፖለቲካ የተርከፈከፈባቸው ነበሩ። በተፈጥሮው በነፃነት የመናገር ተሰጥኦ ስላለው በዘመነ ደርግም ቢሆን፣ ከሌሎች ይልቅ ልቆ ደፍሮ ፖለቲካውን ይነካካ ነበር። ፖለቲካ በቀልድ ሲቀርብ አጥንት ይሰብራል። እንደ ታማኝ ፖለቲካዊ ኩመካ ቢሆን የወያኔ አጥንቶች ከመሰባበር አልፈው ዱቄት መሆን ነበረባቸው። ታማኝ ኩመካውን በመተው ወደ ፖለቲካው ከገባ ወዲህ ብዙ ፈተናዎች ገጥመውታል። አንዳንድ ወዳጆቹ ጠጋ ብለው፣ “ታማኝ! ፖለቲካውን ትተህ ወደ ሙያህ ብትመለስ ይሻልሃል። የሚያምርብህ ኩምክናው ነው” ብለውታል። አንድ ዘመዱ ደግሞ፣ “…ስትናገር አዝማሪ ነኝ ትላለህ። እኛ በዘራችን አዝማሪነት የለብንም። ለምን ስማችንን ታጠፋለህ?” ሲል ጠይቆታል። ቀልድ ሊሆን ይችላል። “ፕሮፌሰርና ዶክተር መውቀስ ታበዛለህ” እያሉ የሚተቹት የመኖራቸውን ያህል፣ “ፕሮፌሰርና ዶክተር ከሚባሉት አንተ ትሻላለህ።” እስከማለት የሚሄዱም አሉ። ደግነቱ ታማኝ በትችቱም ሆነ በሙገሳው የሚሞቀውም ሆነ የሚበርደው አይነት አይመስልም። ባለ አዞ ቆዳ ነው። እንደልቡ ይናገራል። ጠላቶቹም ወዳጆቹም ጓጉተው ያዳምጡታል። “የኔ እውነቶች” የሚለው አባባል አለው። በርግጥ አስቦ ከሚናገረው ይልቅ፣ በስሜት ከልቡ የሚያፈልቀው ይበልጥ ሳቢ ነው። የታማኝ ፈተና የወያኔ ውግዘትና የጥራዝ ነጠቆች ትችት ብቻ አይደለም። ቱባ የሚባሉ ሰዎችን በፖለቲካው ለማነሳሳት በሚያደርገው ጥረት ብዙ ፈተና ይገጥመዋል። ታማኝ ቀረብ እያለ ወደ ስብሰባ ወይም ወደ ተቃውሞ ሰልፍ እንዲወጡ ሲጠይቃቸው እንዲህ የሚል ምላሽ የሚሰጡት አሉ፣ “አዲሳባ ላይ ቤት መስራት ጀምሬያለሁ። በቪዲዮ የምታይ ከሆነ አስቸጋሪ ነው። ሊተናኮሉኝ ይችላሉ። በአሳብ ግን አብሬያችሁ ነኝ። ለማንኛውም ሞት ለወያኔ!” ሌሎች ደግሞ፣ “ምን መሰለህ ታማኝ!? በዚህ ገፈርሳ አካባቢ መሬት ወስጃለሁ። ለዶሮ እርባታ ነው ያሰብኳት። አጥሯን አጥሬ እስክጨርስ ገለል ማለት ይሻላል። የምትሰሩትን ግን እደግፋለሁ። በርቱ! ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!” በርግማን ወያኔ የሞሞት ቢሆን ኖሮ ቀብሩ ገና ድሮ በተፈፀመ። በምርቃት ኢትዮጵያ ለዘልአለም መኖር ብትችልም ይህ ሁሉ ድካም ባላስፈለገ። መቼም እንዲህ ካሉ ፎጋሪዎች ጋር ተባብሮ ወያኔን ማስወገድ ህልም ነው። ታማኝ እንዲህ ባሉ ሰዎች ተከቦ፣ መንፈሱ ባለመርገቡ አደንቀዋለሁ፣ አዝንለታለሁም። በርግጥ ታማኝ ‘ፖለቲከኛ ነኝ’ ብሎ አያውቅም። ርግማን ሆኖብን እንጂ ታማኝ ጊዜውን በፖለቲካ ጉዳይ ማባከን አልነበረበትም። ይቺ “የተረገመች” አገር ተሳክቶላት የሰው ልጅ እንደ ሰው የሚከበርባት አገር ለመሆን ከበቃች ግን፣ መጪው ትውልድ ታማኝን ወደ ነፃነት በሚያመራው መንገድ ላይ እንደ መንገድ ጠራጊ ያስታውሰው ይሆናል…

ዳውድ እና ዱጋሳ…?

የዳውድ ኢብሳና የዱጋሳ በከኮን ኦነግ በሩቅ አጣምሮም ሆነ ለያይቶ ማየት ይቻል ይሆናል። ልዩነታቸውን አቻችለው የቀድሞውን ጠንካራ ኦነግ ወደ ነበረበት ለመመለስ እየሰሩ መሆኑ ይሰማል። የሽማግሎዎችና የወጣት ኦሮሞዎች ግፊት አለበት። “የአንድነት ሃይሎች” ዳውድ ኢብሳን አክራሪ ይሉታል። ለረጅም ጊዜ የኦነግ ሰራዊት ኮማንደር የነበረውን ዱጋሳ በከኮን ቢያውቁት ኖሮ ግን ዳውድን ያመሰግኑት ነበር። ዞሮ ዞሮ ይህ ነባሩ የኦነግ ሃይል እንደገና ተሰብስቦ፣ አንድ ሃይል መፍጠር ከቻለ በቀጣይዋ ኢትዮጵያ ላይ ተፅእኖ የማሳደር አቅሙ ቀላል አይሆንም። ባለፉት 20 አመታት ከቋንቋ እና ኦሮሚያን ክልል ከመመስረት አንፃር የተሰሩ በጎ ስራዎች በኦነግ ግፊት የተፈፀሙ ናቸው። በመሆኑም የኦሮሞ ህዝብ ስነልቦና ከኦነግ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። ከመለስ ስልጣን መልቀቅ ጋር ተያይዞ የኦሮሞ ህዝብ በኦነግ ዙሪያ ሊሰለፍ መቻሉን ማስቀረት የሚቻል አይመስልም። እናም ዳውድና ዱጋሳን በአእምሮ ውስጥ መያዙ የግድ ይላል።

ሃይለማርያም ደሳለኝ….?

ሌላው አማራጭ ራሱ ወያኔ ነው። ኢትዮጵያ የተባለችው አገር በመለስ ዜናዊ እጅ ላይ ያለች አገር እንደመሆኗ ወያኔ፣ “ጥፋ ከዚህ” የሚባልና በቀላሉ የሚገፈተር ሃይል አይደለም። ስልጣን፣ ጠመንጃ፣ ገንዘብና ተንኮል የታጠቀ አደገኛ ሃይል ነው። መለስ እስከ 2015 የአባይ ግድብን በማጠናቀቅ፣ የአዲስአበባን የከተማ ባቡር በማስመረቅ፣ የኑሮ ውድነቱን መቀነስና ኢኮኖሚውን ማረጋጋት ከቻልን እስከ 2030 ስልጣን በእጃችን ይሆናል” እያለ አባላቱን እየሰበከ ይገኛል። በግልባጩ ህወሃት ውስጥ ውስጡን ያልተረጋጋና በቋፍ ላይ ያለ ቡድን መሆኑን ማመን አይፈልግም። የኢኮኖሚ እድገት ቢኖር እንኳ፣ የመብትና የነፃነትን መገፈፍን ሊተካ አይችልም። የሰው ልጅ ለክብሩ እንጂ ለሆዱ አይኖርም። መለስ የመብትና ዴሞክራሲ ጥያቄውን ዘግቶ ሃይለማርያምን በሞግዚትነት ለማንገስ ተዘጋጅቶአል። “ይህን ከማድረግ ሊያስቆመን የሚችል ሃይል የለም” ብሎም ያምናል። በርትተው ሊቃወሙ የሚችሉትን ግለሰቦች ሁሉ በካሮትና ዱላ ስልት ለመቆጣጠር ሙከራውን ቀጥሎአል። እንግዲህ የመለስ የመጀመሪያ ምርጫ ሃይለማርያም ሊሆን ቢችልም፣ ሃይሌ በእግሩ መቆም አቅቶት እንዳይንገዳገድ እነ ደብረፅዮንና ቴዎድሮስ አድሃኖም ታኮ ሆነው ያገለግሉታል። እስከ 2030? ምን ችግር አለው? ህልም ማለም አይከለከልም…

ያልታወቁ ወጣቶች….?

የመለስ ዜናዊን ስልጣን ሊረከቡ የሚችሉ ወጣቶች ወደፊት እየመጡ ይሆን? በቅንጅት የብርቱካን አብዮት ወቅት፣ ትንታግ የነበሩ ወጣቶች አበባማው አብዮቱ ከከሸፈ በሁዋላ አብዛኞቹ ተሰደዋል። የኦነግ ወጣት አባላትም እንዲሁ መሪዎቻቸውን ተከትለው ኮብልለዋል። ህዝብ ግን በርግጥ ተስፋ አይቆርጥም። እንደገና አምጦ ታጋዮችን ይወልዳል። ማን ያውቃል? ገና ያላወቅናቸው የአገር ተስፋዎች ይኖሩ ይሆናል። ምናልባት በኢህአዴግ መዋቅር ውስጥ ያደፈጡ ሊሆኑ ይችላሉ። ምናልባት ደግሞ በሰራዊቱ ውስጥ ያሉ መስመራዊ መኮንኖች! ምናልባት በአንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ ሶስት ሆነው የሚመካከሩ ሻለቆችና ሻምበሎች ይኖሩ ይሆን? እነዚህ ያልታወቁ ወጣቶች ከቶ እነማናቸው? ምናልባት ከትግራይ ይነሱ ይሆን?

በመጨረሻ….?

በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሰላማዊ ፖለቲከኞች ምንም ማድረግ እንደማይችሉ በተደጋጋሚ የታየ ቢሆንም፣ ዞሮ ዞሮ ትግሉ መካሄድ ያለበት ከውስጥ መሆኑ ይታመናል። ርግጥ ነው፣ ልክ እኔ እንደማደርገው እንዲህ ደጅ ሆኖ መለፍለፍ ቀላል ነው። በቀለ ገርባ፣ እስክንድርና አንዷለም ጫማ ውስጥ መግባት ግን እጅግ ከባድ ሊሆን ይችላል። እየወደቁ ወደፊት ከመግፋት በቀር ግን ምርጫ የለም። ያም ሆኖ የእርቅ መንፈስ አስፈላጊነት መቼም ቢሆን ጊዜው አያልፍበትም። ከ50 አመታት በሁዋላ አሁን ስለፖለቲካ የምናወጋው አንዳችንም በህይወት አንኖርም። ተጠራርተንና ተጠራርገን እንወገዳለን። ምን ይሆን ለቀጣዩ ትውልድ ትተንለት የምናልፈው? ቂምና ጥላቻ? የማያባራ ጦርነት? ቅጥፈትና ሌብነት? ሃሜትና ቡጨቃ? ከቶ ምን ይሆን? በመጨረሻ ከተጠቀሱትና ካልተጠቀሱት መካከል “በቀጣይ ኢትዮጵያን የሚመራት ማነው?” የሚለው ጥያቄ በርግጥ አሁንም አልተመለሰም። ሆኖም “የነገው ቀን” በፍጥነት ወደ እኛ እየገሰገሰ ስለሆነ፣ መለስን ማን እንደሚተካ በቅርቡ እናውቀው ይሆናል…